Monday, 16 March 2015

ሰማያዊ ፓርቲ ቅስቀሳ እንዳያደርግ እንቅፋት እየተፈጠረበት ነው

ሰማያዊ ፓርቲ ቅስቀሳ እንዳያደርግ እንቅፋት እየተፈጠረበት ነው • የሶዶ ፖሊስ 8 የሰማያዊ ዕጩዎችን በማሰር ቅስቀሳውን አስተጓጉሏል........ • የጅማ ከተማ የሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት ተዘርፏል ..........• ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ወደ ህዝብ እንዳይደርስ ሆን ተብሎ የተቀየሰ ስልት ነው›› አቶ ስለሽ ፈይሳ ሰማያዊ ፓርቲ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ቅስቀሳ እንዳያደርግ በፖሊሶች ክልከላና ወከባ እየደረሰበት እንደሚገኝ የሰማያዊ ፓርቲ የምርጫ ጉዳይ ኃላፊና ም/ሊቀመንበሩ አቶ ስለሽ ፈይሳ ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ ዛሬ መጋቢት 5/2007 ዓ.ም ፓርቲው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ቅስቀሳ ያደረገ ሲሆን በባህርዳርና ወላይታ ዞን ፖሊስ የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠር ቅስቀሰውን ማደናቀፉን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ዛሬ ሰማያዊ ፓርቲ በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ ቅስቀሳ በሚያደርግበት ወቅት የከተማው ፖሊስ ‹‹የምርጫ ቅስቀሳ አልተጀመረም›› ብሎ ያዋከበ ሲሆን የፓርቲው አመራሮችና አባላት ቅስቀሳ መጀመሩን ገልጸው ስራቸውን እያከናወኑ በነበሩበት ወቅት ‹‹ህገ ወጥ ሰላማዊ ሰልፍ›› አድርጋችኋል በሚል ሌላ ክስ 8 የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎችንና ሌሎች አባላትን በማሰር ቅስቀሳውን እንዳደናቀፈ የወላይታ ዞን የሰማያዊ ፓርቲ ሰብሳቢ አቶ ታደመ ፈቃዱ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ በባህርዳር ከተማ ፖሊስ ‹‹በሞንታርቮ ለመቀስቀስ ፈቃድ ስላላመጣችሁ መቀስቀስ አትችሉም፡፡›› በሚል ፓርቲው ሊያደርገው የነበረውን የምርጫ ቅስቀሳ እንዳደናቀፈ የፓርቲው የምዕራብ ጎጃም ዞን ጊዜያዊ አስተባባሪ አቶ አዲሱ ጌታነህ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ‹ለምን ትከለክሏቸዋላችሁ?› በሚል ህዝቡ ፖሊሶቹን በማፋጠጡ በድምፅ መቀስቀስ ባንችልም በህዝቡ ድጋፍ የቅስቀሳ ወረቀቶችን በማሰራጨት የተሳካ ቅስቀሳ አድርገናል›› ሲሉ አቶ አዲሱ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ወቅት ቅስቀሳ ለማድረግ ምንም አይነት ፈቃድ እንደማያስፈልግ የገለፁት አቶ ስለሽ ፖሊስ የሚፈጥረው እንቅፋት ሆን ተብሎ ሰማያዊ ወደ ህዝብ እንዳይደርስ የተቀየሰ ስልት ነው ብለዋል፡፡ ኃላፊው አክለውም ‹‹የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎችን በመሰረዝ ፓርቲው ምርጫው ላይ የሚፈጥረውን ጫና ለመቀነስ ጥረዋል፡፡ ይህ አልበቃ ሲልም የቅስቀሳ መልዕክቶቻችን በተደጋጋሚ በሚዲያ እንዳይተላለፉ እያደረጉ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ህዝብ እንዳንደርስ በህገ ወጥ መንገድ በፖሊስ ማስቆም ጀምረዋል›› ብለዋል፡፡ በሌላ ዜና የጅማ ከተማ የሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት ባልታወቁ ግለሰቦች መዘረፉን የምርጫ ጉዳይ ኃላፊው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በ02/07/07 ሁለት ሰዓት ላይ አራት ግለሰቦች ጽ/ቤቱን በመስበርና የጽ/ቤቱን ጥበቃ አስፈራርተው በማባረር ለቅስቀሳ የተላከ 6 ሺህ ኦሮምኛ በራሪ ወረቀት እንዲሁም 3 ሺህ አማርኛ በራሪ ወረቀት፣ አንድ የፎቶ ካሜራ፣ አንድ ባነር፣ ለሸካ ዞን ሊላክ የተዘጋጀ 5 ሺህ በራሪ ወረቀት፣ 50 ፖስተር፣ አንድ የእጅ ሜጋ ፎን፣ ሁለት ባነር፣ በርካታ ጋዜጦችና መጽሔቶች ሲዘርፉ የጽ/ቤቱን ኮምፒውተርም ሰብረዋል›› ..........ሲሉ ኃላፊው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

Monday, 9 March 2015

የሰማያዊ ፓርቲ የቅስቀሳ መልዕክት ለአራተኛ ጊዜ በሚዲያ እንዳይተላለፍ ተከለከለ

ኢቢሲ የሰማያዊ ፓርቲን የቅስቀሳ መልዕክት ‹‹አላስተላልፍም›› ብሎ መልሷል • ‹‹ኢቢሲ ከገዥው ፓርቲ ጋር ወግኗል›› አቶ ዮናታን ተስፋዬ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) የሰማያዊ ፓርቲን የቅስቀሳ መልዕክት ‹‹አላስተላልፍም›› ብሎ መመለሱን ዛሬ የካቲት 29/2007 ዓ.ም ለፓርቲው በላከው ደብዳቤ ገልጾአል፡፡ ኢቢሲ በደብዳቤው ‹‹የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በምስሉ ግርጌ የተቀመጠው እንዲሁም በቅስቀሳ መልዕክታችሁ ውስጥ አልፎ አልፎ የሚታየው ሰንደቅ አላማ ምስል የሀገሪቱን ሰንደቅ አላማ የማይወክልና ህገ መንግስቱን…. የሚፃረር ሆኖ አግኝተነዋል›› በሚል እንደማያስተላልፍ ገልጾአል፡፡ በሌላ በኩል ‹‹ይህ የኢቢሲ ተግባር የሰማያዊን ፕሮግራም ላለማስተላለፍ ሆን ተብሎ የተሰጠ ሰበብ ነው›› ያለው የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት አቶ ዮናታን ተስፋዬ በህገ መንግስት የተከለከለውን ቅድመ ምርመራ ኢቢሲ እየተገበረው ነው ሲል ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡ ‹‹ህግ ተጥሷል ከተባለ እንኳን ፕሮግራሙ ከተላለፈ በኋላ እንከሰስ ነበር እንጅ ባልረባ ምክንያት አላስተላልፍም ብለው መመለስ አልነበረባቸውም›› ያለው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ሰንደቅ አላማ የሚውለበለበውን እንጅ ከዛ ውጭ ያለን ማናቸውንም ነገር የሚመለከት አይደለም ሲል ኢቢሲ የፓርቲውን መልዕክት ላለማስተላለፍ ያቀረበውን ሰበብ ተችቷል፡፡ አቶ ዮናታን አክሎም ‹‹በአዋጅ 654/201 ላይ የሰፈረው ህግ አንድም ቦታ ተሰቅሎ ስለሚውለበለብ፣ ከመኪና ከሚውለበለብ እና በአደባባይ ከሚያዝ ሰንደቅ አላማ ውጭ ስለ ሌላ አንዳችም የሚከለክለው ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ኢቲቪ ለገዥው ፓርቲ በመወገን ፕሮግራማችን እንዳይተላለፍ እያደረገ ነው›› ሲል ወቅሷል፡፡ በተያያዘ ዜና ፓርቲው ነገ የካቲት 30 በሬድዮ ፋና ከአንድ ሰዓት ዜና በኋላ ለሚተላለፈው ፕሮግራም ትናንት ስድስት ሰዓት መልዕክቱን ለራዲዮ ጣቢያው ለማስገባት ቢሞክርም ‹‹ዘግተው ወጥተዋል፣ ሰኞ ነው የሚገቡት፡፡ ሰኞ አስገቡ›› በሚል የሰማያዊ ፓርቲን መልዕክት መልሰዋል፡፡የፓርቲዎች መልዕክት ከሚተላለፍበት 36 ሰዓት ቀድሞ እንዲገባ እንደተባለ የገለጸው አቶ ዮናታን ሰኞ ጠዋት የሚተላለፍን መልዕክት ‹‹ሰኞ ጠዋት አምጡ›› ብሎ መመለስ ላለማስተላለፍ እንደወሰኑ ያሳያል ብሏል፡፡ ከአሁን ቀደም ኤፍ ኤም 96.3 ሁለት ጊዜ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሬድዮ አገልግሎት አንድ ጊዜ የሰማያዊ ፓርቲን የቅስቀሳ መልዕክት የመለሰ ሲሆን ይህኛው ለአራተኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡

Monday, 2 March 2015

በአዲስ አበባ የመኪና አደጋው በፎቶ ግራፍ

ዘ-ሐበሻ በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተከሰቱ ስላሉ የመኪና አደጋዎች እርምት እንዲወሰድ ከሚል አንፃር ስትዘግብ ቆይታለች:: በኢትዮጵያ ባፈለው ዓመት ብቻ ከ3 ሺህ በላይ ዜጎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸው ሲያጡ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሟል። ከዚህ ውስጥ 3 ሺህ 331 ሰዎች በአደጋው ህይወታቸውን ሲያጡ ከ11 ሺህ በላይ ደግሞ ለከባድና ለቀላል የአካል ጉዳት መዳረጋቸው ተዘግቧል፡፡ የኢትዮጵያ ትራፊክ ፖሊስ ባወጣው መግለጫ ደግሞ በኢኮኖሚው ላይ እያሳደረ ያለው ጉዳት ከባድ ነው ይላል;; ዝርዝሩን ያንብቡ
ዘ-ሐበሻ) በኢትዮጵያ በየቀኑ እየደረሱ ያሉ የመኪና አደጋዎች ቁጥር ከ እለት ወደ እለት እየጨመረ መሄዱ ነዋሪዎችን በከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደከተተ የዘ-ሐበሻ ዘጋቢዎች ይናገራሉ:: በዚህ በዘ-ሐበሻ ድረገጽ ላይ እንኳ በጊዜው ስለመኪና አደጋዎችና ስለሚወድመው የሰው ሕይወትና ንብረት በተደጋጋሚ ጽፈናል:: አሁን ደግሞ ከአዲስ አበባ የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው አራት ኪሎ የድል ሐውልት አደባባይ አካባቢ ከስድስት ኪሎ መስመር ወደ ለገሀር ይጓዝ የነበረ የአንበሳ ከተማ አውቶቡስ ባገጠመው የፍሬን ችግር ከአንድ ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ የሁለቱም ተሽከርካሪ ሹፌሮች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል:: በዚህ የመኪና አደጋ በተሳፋሪዎች ላይ የደረሰ ጉዳት ባይኖርም አደጋው በፎቶ ግራፍ ላይ እንደምትመለከትት በጣም አሰቃቂ ነበር:: ከስድስት ኪሎ ከሚገኘው ቤታቸው ሃገር አማን ብለው ወደ ሥራቸው በማሽከርከር ላይ የነበሩትና ጉዳት የደረሰባቸው አቶ ግርም ጎርፉ የተባሉ ግለሰብ የአንበሳ አውቶቡሱ ድንገት መስመሩን ስቶ በመምጣት እንደገጫቸው ገልጸዋል::
....በአዲስ አበባ አንበሳ አውቶቡሱ መንገድ ስቶ የቤት መኪናውን ገጨ... ዘ-ሐበሻ) በአዲስ አበባ ከተማ ከካራ ቆሬ ወደ ለገሃር ሲጓዝ የነበረ አውቶቡስ ዘነበወርቅ አለርት ሆስፒታል ፊትለፊት ረዥም ድልድይ ውስጥ ገባ፤ በዚህ አሰቃቂ አደጋ ስምንት ሰዎች መሞታቸው ይፋ ሆነ። አውቶቡሱ ቁጥራቸው እስካሁን በውል ያልታወቁ ተሳፋሪዎችን ጭኖ ይጓዝ የነበረ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ሲያስታውቅ የአውቶቡሱ ቁጥር 66 እንደሆነ ታውቋል። ካራ ቆሬ ወደ ለገሃር ሲጓዝ ዘነበወርቅ አለርት ሆስፒታል ፊት ለፊት ባለው ረዥም ድልድይ ውስጥ በገባው አውቶቡስ የተነሳ በአደጋው እስካሁን አንድ እግረኛን ጨምሮ አራት ወንድ እና አራት ሴት ተሳፋሪዎች ህይወታቸው እንዳለፈ ሲገለጽ 46 የሚሆኑት ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ዘ-ሐበሻ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል። የአውቶቡሱ ሹፌር እና ትኬት ቆራጭ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በሕይወት ተርፈዋል። የአውቶቡሱ አደጋው መንስኤ ላይ መሆኑ ሲታወቅ በአውቶቡሱ ድልድይ ውስጥ መግባት ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑ ዘ-ሐበሻ ጨምሮ የደረሳት ዜና ያስረዳል።
....ዘነበወርቅ ድልድልይ የገባው አውቶቡስ ሲወጣ