Friday, 14 November 2014

ኦባንግ ስለ ሁለተኛው የአፍሪካ መሬት ነጠቃ

o meth o

“ድርጊቱ የሚፈጸመው በእንግሊዝ ዕርዳታ ነው” አሉ

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ በሥራ ጉዳይ እንግሊዝ አገር ተገኝተው የነበሩት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ ሎንዶን የሚገኘው Minority Rights Group International ጽ/ቤት ባደረገላቸው ግብዣ ቃለምልልስ አድርገው ነበር፡፡

በቃለምልልሱ ወቅት ሁለተኛው የአፍሪካ የመሬት ነጠቃ እየተካሄደ እንደሆነ እና እንዲህ ዓይነቱ አስከፊ ተግባር እየተፈጸመ ያለው በእንግሊዝና ሌሎች ምዕራባውያን አገራት ዕርዳታና ድጋፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ የአናሳ ቡድኖች መብት አይከበርም የሚባልበት ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ያለው እነዚህ ወገኖች መብት የሚባል ነገር እንደሌላቸው አቶ ኦባንግ ተናግረዋል፡፡ እንደ ማስረጃም በጋምቤላ አካባቢ መሬታቸውን በግፍ እየተነጠቁ ለስደት፣ ለግዳጅ ሰፈራ፣ ይህንንም የተቃወሙ ለስደት፣ እስራትና ግድያ የተጋለጡትን በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡
በጋምቤላ ያለውን ሁኔታ ሲያስረዱም “በጋምቤላ ያለው ድህነት ለዘመናት ድርቅ ሲያጠቃው እንደኖረው የሰሜኑ ክፍል የሞቱ ላሞች፣ የኮሰሱ ህጻናት፣ የሚበሉት ያጡ ሰዎች የሚታዩበት አይደለም፡፡ እንዲያውም ጋምቤላ ከኢትዮጵያ ክፍሎች እጅግ ለም የሆነው ነው” በማለት አስረድተዋል፡፡ ነገርግን በክልሉ ያለው የዜጎች ንብረት ለሰፋፊ እርሻዎች እንዲሆኑ ለባለሃብቶች በመሰጠቱ እነዚህም ባለሃብቶች ያለገደብ በመሬት ነጠቃ ላይ በመሳተፋቸው የክልሉ ሕዝብ ለከፍተኛ ችግር መጋለጡን በቃለምልልሱ ማስረጃዎችን እየጠቀሱ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡
“146ሺህ ሔክታር የኢትዮጵያን ለም መሬት ለ99ዓመት በ99ሳንቲም ሊዝ ለመስጠት መስማማት ያውም ይህንን ዓይነቱን ውሳኔ ነዋሪውን ሕዝብ ሳያማክሩ ማድረግ እኤአ በ1884 የበርሊኑ ኮንፍራንስ አፍሪካን ከተቀራመቱት አውሮጳውያን ድርጊት ምንም ተለይቶ አይታይም” በማለት ያስረዱት የጋራ ንቅናቄው ዋና ዳይሬክተር የዚያን ጊዜ አውሮጳውያኑ ውሳኔውን ሲያስተላልፉ አፍሪካውያን በጠረጴዛው ላይ ባለመኖራቸው አፍሪካውያኑ እስካሁን የዚያ ዕዳ ከፋዮች ሆነው መቅረታቸውን “ጥቁር ሰው” ኦባንግ ሜቶ ተናግረዋል፡፡ “አሁንም” ይላሉ ሲቀጥሉ “አሁንም በሕዝብ ያልተመረጡ የአፍሪካ አምባገነኖችን (ነዋሪውን ሕዝብ ሳያማክሩ) መሬት እየነጠቁ፣ የተፈጥሮ ሃብት እየዘረፉ” እንደሆነ በግልጽ አስረድተዋል፡፡
ከምዕራባውያን መንግሥታት 3.1ቢሊዮን ዶላር የሚያገኘው የኢህአዴግ አገዛዝ የፈለገውን እንዲያደርግ ከአለቆቹ የተፈቀደለት እንደሚመስል በመናገር ምዕራባውያን በገሃድ ለሚታየው የሰብዓዊ መብት ረገጣ ዓይናቸውን መጨፈናቸው በኢትዮጵያ ቀኑን ጠብቆ የሚፈነዳ ቦምብ እንዲኖር የፈቀዱ ያህል መሆኑን አቶ ኦባንግ ተናግረዋል፡፡ ሲቀጥሉም “መፍትሔው ሰላማዊ ትግል ነው፤ ምክንያቱም በኢትዮጵያ በሥልጣን ላይ ያሉትና ሁሉንም ነገር የሚቆጣጠሩት የትግሬ አናሳዎች በመሆናቸው የዘር እሣተጎመራ ከፈነዳ የሚሆነውን ለመገመት እንኳን አይቻልም” በማለት አሁንም ለችግሩ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ከዓመጽ ነጻ የሆነ ትግል ማድረግ ብቻ እንደሆነ በአጽዕኖት አስረድተዋል፡፡
አቶ ኦባንግ ሜቶ ባደረጉት ቃለምልልስ ላይ የተጠናቀረው ዘገባ ሙሉ ቃል የሚከተለው ነው፡-
Read more:- http://www.goolgule.com/ethiopia-obang-metho-condemns-life-grabs-and-the-second-scramble-for-africa/

No comments:

Post a Comment