Tuesday, 24 February 2015
የኬንያ ፖሊስ 101 ኢትዮጵያዉያንን አሠሩ
ናይሮቢ፤ የኬንያ ፖሊስ 101 ኢትዮጵያዉያንን ማሠሩ
የኬንያ ፖሊስ በሕገወጥ መንገድ ወደደቡብ አፍሪቃ ሊጓዙ ነበር ያላቸዉን ከመቶ የሚበልጡ ኢትዮጵያዉያንን ትናንት ማምሻዉን ማሠሩን አሶሲየትድ ፕረስ ከናይሮቢ ዘገበ። የኬንያ ልዩ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ኖህ ካቱሞ ለዜና ወኪሉ ዛሬ እንደገለፁት የታሠሩት 101 ወንዶች ኢትዮጵያዉያንና እነሱን በኬንያ ድንበር በኩል ሊያሾልኩ በመሞከር የተጠረጠሩ ሶስት ኬንያዉያን ናቸዉ። ካቶሙ እንዳሉት ኢትዮጵያዉያኑ ወደደቡብ አፍሪቃ ጉዟቸዉን ከመቀጠላቸዉ በፊት በቡድን በቡድን ሆነዉ ኬንያ መዲና ናይሮቢ በሚገኝ አንድ ቤት ዉስጥ አርፈዉ ነበር። ታሳሪዎቹ ዳኛ ፊት ቢቀርቡም እንግሊዝኛ ስለማይረዱና በአማርኛም የሚያስተረጉምላቸዉ ባለመገኘቱ ምክንያት ለጊዜ ክስ አልተመሠረተባቸዉም። እንደዘገባዉ ዳኛዉ ቪክቶር ዋኩሜሌ አስተርጓሚ እስኪገኝ ጉዳዩን ለነገ ቀጥረዋል። ከዚህ ቀደምም ለተመሳሳይ ጉዞ የተዘጋጁ 95 ኢትዮጵዉያን በኬንያና ታንዛንያ ድንበር አቅራቢያ መታሠራቸዉ ተዘግቧል። የኬንያ ፖሊስ ከአፍሪቃ ቀንዷ ሀገር ሰዎችን የሚያሸጋግሩት ወገኖች ኢትዮጵያዉያኑን በሕገ ወጥ መንገድ የሚያዘዋዉሩት የጦር መሣሪያ፣ አደንዛዥ እፆች፣ የዝሆን ጥርስና የመሳሰሉትን ነገሮች አስርገዉ በሚያስገቡበትና በሚያወጡበት መስመር እንደሆነ ገልጿል። ...... source.-www.dw.amharic
ከሜድትራኒያን ሞት ፊት የቆሙት ስደተኞች
ባለፈው የጎርጎሮሳውያኑ አመት የሜድትራኒያን ባህርን በጀልባ ለማቋረጥ ከሞከሩ 218,000 ሰዎች መካከል 3,500 መሞታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን አስታውቋል። በዚህ በተመሳሳይ መንገድ ወደ አውሮጳ ለመሻገር የሚሞክሩ ስደተኞች ቁጥር በአሳሳቢ ደረጃ በመጨመር ላይ ነው።
ሰለሞን መንግስቴ በሊቢያዋ የቤንጋዚ ከተማ ባለቤቶቹ ጥለውት የሄዱትን ቤት ይንከባከባል።አትክልት ይኮተኩታል። ግቢውን ያጸዳል። ሰለሞን በቤንጋዚ ብቻውን አይደለም። ባለቤቱ የዝና እዘዘው ቀን ቀን ከሰው ቤት ትሰራለች። ሰለሞን ስለ ወርሃዊ ደሞዙ ሲጠየቅ ፈገግ እያለ «በእውነት መቼ እንደሚከፍሉኝም አላወኩም።» ሲል ይመልሳል።
ሰለሞን ተወልዶ ካደገበት የጎንደር አካባቢ ወደ ሱዳን ገዳሪፍ የተጓዘው ለደላሎች አምስት ሺ የኢትዮጵያ ብር ከፍሎ በአስቸጋሪ የሌሊት ጉዞ ነበር። ጉዞውን ያመቻቹለት የኢትዮጵያ እና የሱዳን ህገ-ወጥ ደላሎች ነበሩ። «ጉዞው የሚጀመረው ለሊት ሰው በሌለበት ሰዓት በእግር ነው። የሚለው ሰለሞን መንገዱ ከሶስት እስከ ሰባት ቀናት ሊወስድ እንደሚችል ይናገራል። ከገዳሪፍ በኋላ በመኪና የሚደረገው ጉዞ «ሰው በሰው ላይ ጭነው ስለተጓዝን በእግር ከተደረገው የበለጠ ያስከፋል።»ሲል ያስታውሳል።
በተመሳሳይ መንገድ ከኢትዮጵያ ከወጣችው ከባለቤቱ የዝና እዘዘው ጋር የተዋወቁት በሱዳን በቤተ-ክርስቲያን ነበር። ሁለቱ ስደተኛ ወጣቶች መስከረም 5 ቀን 2006 ዓ.ም. ሶስት ጉልቻ መሰረቱ። ከ2003-2006 ዓ.ም. የዝና በሰው ቤት ሰለሞን ተመላላሽ ስራ እየሰሩ ቢቆዩም ሃገሩ አልተመቻቸውም። እንደገና ሌላ መንገድ-ሌላ ጉዞ አሁንም በህገ-ወጥ መንገድ
ከሱዳን ወደ ሊቢያ ለመጓዝ ለህገ-ወጥ ደላሎች በነፍስ ወከፍ ስድስት ሺ በአጠቃላይ አስራ ሁለት ሺ የሱዳን ፓውንድ ከፍለዋል። ሰለሞን ከባለቤቱ ጋር ከሱዳን ተነስተው የሰሐራ በርሃን ሲቋርጡ ጉዞውን ያመቻቹትን ሰዎች «አይን ያወጡ ደላሎች » ሲል ይገልጻቸዋል። 9.4 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሰፋውን የሐራ በርሃ ማቋረጥ ለጥንዶቹ መራር ነበር። «አንዲት ዛፍ ለውርርድ የማታይበት» ይለዋል ሰለሞን የሰሐራ በርሃን። የዝና እዘዘው ከሱዳን ወደ ሊቢያ ላደረጉት ጉዞ ዋንኛ ምክንያታቸው «ዞሬ ወደ አገሬ ብመለስ ምን ይዤ ልመለስ? » የሚለው ጥያቄ ትልቅ ቦታ እንደነበረው ታስታውሳለች። ስምንት ቀናት የፈጀውን ጉዞ ስታስታውስ ሲቃ ይተናነቃታል። ከበርሐው ንዳድ እና ውሃ ጥም ባሻገር ከውስጧ ሃዘን የቀበረ ትዝታ አላት። « ስንት እህቶቻችንን በበርሐ ጥለናቸው መጥተናል። እህቴ ወንድሜ አትልም። እህቴ ተኝታ ብትቀር አትቀሰቅስም።» ስትል ስለተሻገረችው የበርሐ ሞት ትናገራለች። ከሱዳን ወደ ሊቢያ በነበረው ጉዞ ስደተኞችን ከጫኑ ሶስት መኪኖች መካከል አንዱ ተገልብጦ ብዙዎች ማለቃቸውን ሰለሞን ያስታውሳል።
ሰለሞን እና እዝና የሰሐራ በርሃን አቋርጠው ሊቢያ ሲገቡ ከለበሱት ልብስ በቀር በእጃቸው አንዳች ነገር አልነበረም። ውስን ምግብ፤አልባሳት እና የግል ንበረቶች የያዙባቸው ሻንጣዎች መንገድ መቅረታቸውን እዝና ተናግራለች። እናም ሁለቱ ወጣት ጥንዶች ሊቢያ ሲደርሱ ፓስፖርትም ይሁን የጉዞ ሰነድ በእጃቸው አልነበረም።
የሊቢያ ሁለተኛ ከተማ የሆነችው ቤንጋዚ እንደ ቀድሞ ሰላም እና መረጋጋት ርቋታል። ነዋሪዎቿ የመኖሪያ ቤታቸውን ጥለው ተሰደዋል።ሰለሞን እና የዝና በቤንጋዚ የበረከተው የጥይት ተኩስ እና ሞት ስጋት ፈጥሮባቸዋል። እናም ሜድትራኒያን ባህርን ተሻግረው አውሮጳ ሊገቡ ቆርጠዋል።ሰለሞን «አሁን ካለንበት ቢንጋዚ የእቃ መርከብ ይመጣል ይባላል። ግን አይገኝም። እሱ 1,500 ዶላር ነው። ከደላላው ጋር ተነጋግረናል። በመጣ ጊዜ እነግራችኋለሁ ብሎናል።» ሲል የመጀመሪያ አማራጫቸውን ያስረዳል። ሁለተኛ አማራጫቸው አሁን ካሉበት ቤንጋዚ ከሊቢያዋ ዋና ከተማ 50 ኪ.ሜ. ወደ ምትርቀው ጋሪቡሊ መጓዝ ይኖርባቸዋል።«ከጋሪቡሊ ትልቅ የሚባለው እስከ 1,500 ዶላር የሚከፈልበት ነው። መካከለኛ የሚባለው ከ900-1100 ዶላር የሚከፈልበት ሲሆን አነስተኛ የሚባለው እና ብዙ ጊዜ አደጋ ደረሰባት የሚባለው ጀልባ ጉዞ ሰባት መቶ እና ስምንት መቶ ዶላር ያስከፍላሉ።» የሚለው ሰለሞን ጉዞው አስራ ስምንት ሰዓታት እንደሚወስድም መረዳታቸውን ተናግሯል።
ሰለሞንም ሆነ እዝና በጉዞው ስለሚገጥማቸው መከራ ጠንቅቀው ያውቃሉ። እዝና ከለቅሶዋ ጋር እየታገለች ሌላ ምንም አማራጭ እንደሌላቸው ታስረዳለች። «ምን ይዤ?» ከሚለው የኢኮኖሚ ጥያቄ ባሻገር በእጃቸው የጉዞ ሰነድ ባለመኖሩ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ቢያስቡ እንኳ ያለፉበትን መራራ ጉዞ መድገም ይኖርባቸዋል።ሰለሞን «አቅጣጫ የመሳት፤የመናወጥ፤ብርድ፤የመገልበጥ እና የመዋጥ ችግር እንዳለ እንሰማለን። እንዲህ አይነት እጣም የሚደርሳቸው ሰዎች እንዳሉ እንያወቅን ነው። ከሞት ጋር እየተነጋገርን ነው ማለት ትችላለህ።» ሲል ተናግሯል።
በዚህ ወር ብቻ ከሊቢያ ወደብ ተነስተው የሜድትራኒያን ባህርን በማቋረጥ ወደ ጣሊያን ለመሻገር የሞከሩ 300 ስደተኞች ለሞት ሳይደረጉ እንዳልቀረ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን አስታውቋል። ባለፈው አመት ብቻ 218,000 ሰዎች የሜድትራኒያን ባህርን በጀልባ አቋርጠዋል። 3,500 ያህሉ ግን ከጉዞው መጨረሻ መድረስ ሳይችሉ በባህሩ ላይ ህይወታቸውን አጥተዋል። ሰለሞን እና የዝና በጉዞው ሊገጥማቸው የሚችለውን ሁሉ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ቢሆንም ፓስፖርትም ይሁን ህጋዊ የጉዞ ሰነድ በእጃቸው ባይኖርም ጉዞ ለመጀመር ዝግጅት ላይ ናቸው።
እሸቴ በቀለ
ሒሩት መለሰ
Saturday, 21 February 2015
ሰበር ዜና – የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በዕጩነት እንዳይቀርቡ ተደረገ
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በዕጩነት እንዳይቀርቡ ተደረገ
‹‹ምርጫ በህዝብ ፍላጎት ሳይሆን በሎተሪ ሆኗል›› ኢ/ር ይልቃል ጌትነት አዲስ አበባ ከተማ ወረዳ 5 ለመጭው ምርጫ ለተወካዮች ምክር ቤት ሰማያዊ ፓርቲን ወክለው ሊቀርቡ የነበሩት የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ‹‹ከቀረቡት 17 ዕጩዎች መካከል በተጣለ ዕጣ ወድቀዋል›› በመባላቸው ለመጭው ምርጫ በዕጩነት እንዳይቀርቡ መደረጋቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ኢ/ር ይልቃል በዕጩነት በቀረቡበት ወረዳ 5 የምርጫ ጣቢያ ኢህአዴግ፣ የትግስቱ አንድነት፣ ቅንጅትን ጨምሮ ሌሎች ስድስት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ያለ ምንም ዕጣ አልፈዋል የተባለ ሲሆን ‹‹የሚያልፉት በዕጣ ነው›› የተባሉት ሰማያዊን ጨምሮ 11 የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች መካከል ሰማያዊና ሌሎች አራት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ‹‹ዕጣ አልወጣላቸውም፡፡›› ተብሏል፡፡ ስለ ጉዳዩ ያነጋገርናቸው የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ‹‹ሰማያዊ ህዝብ ውስጥ በሰፊው እየገባና እያንቀሳቀሰ ያለ ግንባር ቀደም ፓርቲ ነው፡፡ እንደ ኢህአዴግ ያሉን ጨምሮ ዕጣ ውስጥ አይገቡም፡፡ ሰማያዊ ደግሞ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ከማያደርጉት ፓርቲዎች ጋር ዕጣ ውስጥ ገብቶ ወደቀ መባሉ ዴሞክራሲ ከጅምሩ ጀምሮ የህዝብ ድምጽ ሆኖ እያለ በእኛ አገር ሎተሪ ሆኗል ማለት ነው፡፡›› ብለዋል:: ሊቀመንበሩ አክለውም ‹‹ሂደቱ ምንም ይሁን ምን አንድን ፓርቲ ወይንም ተወካይን ህዝብ ነው መምረጥ ያለበት፡፡ ህዝብ የሚፈልገውና የሚመረጥ ፓርቲ ነው ለምርጫ መቅረብ ያለበት፡፡ አሁን ግን እየተባለ ያለው በአንድ በኩል ህዝብ የማይፈልገው ያለ ዕጣ ሲገባ፣ በሌላ በኩል ህዝብ የሚፈልገው ሰማያዊን የመሰለ ፓርቲ ዕጣ ውስጥ ገብቶ አላለፈም እየተባለ ነው፡፡ በአንድ በኩል ህዝብ የተማረረባቸው ያለ ቅድመ ሁኔታ ህዝብን እንደሚያንቀሳቅስ የሚታወቀው ሰማያዊ ደግሞ ህዝብ ስፈለገው አሊያም በጥንካሬው ሳይሆን በሎተሪ ወድቀሃል ተብሏል›› ሂደቱ የተሳሳተ ነው ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/

Thursday, 12 February 2015
አቶ ጸጋዬ አላምረው የእሥር ማዘዣ በመዉጣቱ አገር ለቀው ተሰደዱ
የእሥር ማዘዣ በመዉጣቱ አቶ ጸጋዬ አላምረው አገር ለቀው ተሰደዱ
የአንድነት ፓርቲ ምክትል አፈጉባኤ የሆኑትና በቅርቡ ሰማያዊ ፓርቲ የተቀላቀሉት አቶ ጸጋዬ አላምረው፣ ከወያኔ የፀረ-ሽብር ግብረ ኅይል እንዲታሰሩ የማዘዣ ወረቀት በመዉጣቱ፣ ለተወሰነ ቀናት አገር ቤት ራሳቸውን ሰዉረውከቆዩ በኋላ፣ በአሁኑ ጊዜ ከኢትዮጵያ ዉጭ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።
አቶ ጸጋዬ የአንድነት ፓርቲ የፋይናንስ ሃላፊ ሆነው የሰሩ ሲሆን፣ አቶ ሃብታሙ አያሌው ከታሰሩ በኋላ የመኢአድ አመቻች ኮሚቴ ዋሃ ሰብሳቢ ሆነው ሰርተዋል።፣ ሕወሃቶች መሰናክል ፈጠርበት እንጂ በመኢአድ እና በአንድነት መካከል ዉህደቱ ጫፍፍ እንዲደርስ፣ ቁልፍ ሚና ከተጫወቱ የአመራር አባላት መካከል አንዱ ነበሩ። የአንድነት ፓርቲ ያደርግ በነበረው የምርጫ ዘመቻም፣ የምርጫ ኮሚቴ አባል በመሆን ትልቅድርጅታዊ ሥራ ይሰሩም ነበር።
የአንድነት ፓርቲ በአዲስ አበባ ጠርቶት በነበረው ሰልፍ ፣ የሕወሃት ታጥቂዎች በሰላማዊ ዜጎችን ላይ ኢሰባአዊ የሆነ ከፍተኛ ድብደባ በፈጸሙበት ወቅት፣ በአካል ከተጎዱት ወገኖች መካከል አንዱ አቶ ጸጋዬ ነበሩ። ከስድስት ወራት በፊትም በግንቦት ወር 2006 ዓ.ም፣ አንድነት እና መኢአድ የቅድመ ዉህደት ፊርማ በፈረሙበት ጊዜም፣ የአገዛዙ ካድሬዎች ስብሰባዉ ለመረበሽ በሞከሩበት ወቅት ተፈንክተው ትልቅ ጉዳት ደሮባቸውም ነበር።
ሕወሃቶች በአቶ ጸጋዬ ላይ ያነጣጠሩት፣ በርካታ የአንድነት አባላትን ይዘው አቶ ፀጋዬ ሰማያዊን ከተቀላቀሉ በኋላ ሲሆን፣ ዋና ክስ አድርገው የወሰዱትም “አንድነት ፓርቲ የገንዘብ እርዳታ ከሽብርተኞች ይቀበላል፣ የሚቀበለዉም በአቶ ጸጋዬ አላምረው በኩል ነበር” የሚል እንደሆነ ታውቋል። ሕወሃቶች በሚቆጣጠሩት ኢቲቪና ራዲዮ ፋና ከፍተኛ የስም ማጥፋት ዘመቻ በአንድነት ላአይ የጅመሩ ሲሆን፣ እነ ትግስቱ አወሉንም በሜዲያ፣ የአቶ ጸጋዬ አላምረዉን ስም እየጠሩ “ገንዘብ ተቀባይ እርሱ ነበር” እያሉም እንዲናገሩ እያደረጓቸው ነው።
የአንድነት ፓርቲ በዉጭ አገር ካሉ ኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ያገኝ እንደነበረ ይታወቃል። በዉጭ ያሉ የአንድነት ድጋፍ ድርጅቶችም፣ ከቅንጅት ጊዜ ጀምሮ በሰማዊ ትግል የሚያምኑ እንደመሆናቸው፣ በነርሱ በኩል ተሰብስቦ የሚላክን ገንዘብ ከሽብርተኞች እንደመጣ አድርጎ መቁጠር በሕግ፣ በሞራልም በአሰራር ተቀበያነት እንደሌላው የድጋፍ ድርጅቱ አባላት ይናገራሉ።
- source,-www.zehabesha.com
Wednesday, 11 February 2015
በዩኒቨርሲቲው ጥበቃ የአንዱ ተማሪ ሕይወት አለፈ
በዩኒቨርሲቲው ጥበቃ ከተደበደቡት ተማሪዎች መካከል የአንዱ ሕይወት አለፈ
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለው በምርመራ ላይ ናቸው
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አካባቢ በሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ፋኩልቲ፣ ሁለት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው የጥበቃ ሠራተኛ ድብደባ ተፈጽሞባቸው አንደኛው ሕይወቱ ማለፉ ተረጋገጠ፡፡
ጥር 23 ቀን 2007 ዓ.ም. የግማሽ ዓመት ፈተናቸውን ካጠናቀቁት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መካከል፣ ሙሉቀን ከበደና ታምራት አባተ የተባሉ ተማሪዎች በዕለቱ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ታውቋል፡፡ ተማሪዎቹ ፈተናቸውን እንዳጠናቀቁ ከግቢ ወጥተው ሲዝናኑ ካመሹ በኋላ ወደ ማደሪያ ክፍላቸው ሲመለሱ፣ ፀደቀ አድማሱ ከሚባለው ተጠርጣሪ የጥበቃ ሠራተኛ ጋር መጋጨታቸውን ከፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ተማሪዎቹ ወደ ዩኒቨርሲቲው ግቢ ሊገቡ ሲሉ ተጠርጣሪው እንዲቆሙ ሲያደርጋቸው ተማሪ መሆናቸውን የሚያረጋግጡበትን መታወቂያ ቢያሳዩም፣ ከተጠርጣሪው ጋር ሊግባቡ ባለመቻላቸው ድብድቡ መጀመሩ ታውቋል፡፡ ተጠርጣሪው በወቅቱ ይዞት በነበረው የእንጨት ዱላ ደጋግሞ ሲደበድባቸው የተመለከተ ሾፌር፣ ሌሎች የተኙ ጥበቃዎችን በማስነሳቱ የተፈጠረው ድብድብ የቆመ ቢሆንም፣ ተማሪዎቹ በደረሰባቸው ድብደባ ተጎድተው ስለነበር በአቅራቢያቸው በሚገኘው ጥሩነሽ ቤጂንግ ጠቅላላ ሆስፒታል መወሰዳቸውም ተጠቁሟል፡፡
ታምራት አባተ የተባለው ተማሪ በጥሩነሽ ቤጂንግ ጠቅላላ ሆስፒታል በተደረገለት ሕክምና የተረፈ ቢሆንም፣ የደረሰበት ድብደባ ከባድ በመሆኑ ለተጨማሪ ሕክምና ሪፈር የተደረገው ተማሪ ሙሉቀን፣ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሕክምና ላይ እያለ ጥር 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ሕይወቱ ማለፉ ታውቋል፡፡ ፖሊስ በድብደባው ተሳትፈዋል በማለት በቁጥጥር ሥር ያዋላቸውን ተጠርጣሪ የዩኒቨርሲቲውን የጥበቃ ሠራተኞችን ፍርድ ቤት አቅርቦ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመጠየቅ በምርምራ ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡
- See more at: http://satenaw.com/amharic/
Tuesday, 10 February 2015
አባዱላ ገመዳ የሃሰት ዲግሪዎችን ሸምተው መጠቀማቸው ተረጋገጠ
አበበ ገላው በአባዱላ ገመዳ 2 የውሸት ዲግሪዎች ግዢ ዙሪያ ማስረጃዎችን ለቀቀ
(አዲስ ቮይስ) የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ የሆኑት አባዱላ ገመዳ በኢንተርኔት ያለምንም ትምህርት ዲግሪ በመሸጥ ከሚታወቅ አንድ የዲፕሎማ ወፍጮ ቤት (diploma mill) የሃሰት ዲግሪዎችን ገዝተው መጠቀማቸውን አዲስ ቮይስ አረጋገጠ።
አፈጉባኤው የባችለርስ ዲግሪ እ.ኤ.ኤ በ2001 እንዲሁም የማስተርስ ዲግሪ በ2004 አሜሪካን አገር በሚኖረውና አሊ ሚርዛኢ በሚባል ኢራናዊ ከሚንቀሳቀሰው “አሜሪካን ሴንቸሪ ዩኒቨርሲቲ” (ሴንቸሪ ዩኒቨርሲቲ) ያለምንም ትምህርት መግዛታቸው በመረጃ ተረጋግጧል። አባዱላ ሁለቱንም ዲግሪዎች የህዝብ አስተዳደር ትምህርት ተምረው አንዳገኟቸው ሲገልጹ የቆዩ ሲሆን ይህንንም በፓርላማ ድረገጽ፣በፌስቡክ፣ ዊኪፔድያ፣ በመንግስትና በግል የመገናኛ ተቋማት በይፋ ታትሞ እንዲሰራጭ አድርገዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከቻይና መከላከያ ዩኒቨርሲቲ የባችለርስ ዲግሪ እንዳገኙ በህይወት ታሪካቸው ላይ በይፋ ያሰፈሩ አባዱላ እንዲህ አይነት ዲግሪም ይሁን ትምህርት ከቻይና የትምህርት ተቋም አለማግኘታቸው ታውቋል።
ሴንቸሪ ዩኒቨርሲቲ ከማንም እውቅና ያልተሰጠው ሲሆን አሊ ሚርዛኢ በዋነኛነት ከቤቱ የዲግሪ ሽያጭ እንደሚያከናውን አዲስ ቮይስ በምርመራው ከማረጋገጡም በላይ ምርመራውን ደንበኛ መስሎ ላካሄደው ጋዜጠኛ አበበ ገላው የማስተርስና የዶክትሬት ዲግሪዎችን በ4000 ዶላር ሊሸጥለት ሞክሯል። ይህንንም ህገወጥ የዲግሪ ሽያጭ የሚያረጋግጡ በርካታ የኢሜይልና የሰነድ መረጃዎች ጋዜጠኛው እጅ ገብተዋል።
ከሁለት ሳምንታት በፊት የህወሃቶች ቁንጮ ምሁራን ተደርገው ይቆጠሩ ከነበሩት አንዱ ቆንስጣንጢኖስ በርሄ የማስተርስና የዶክትሬት ዲግሪ ከሴንቸሪ ዩኒቨርሲቲ ገዝተው እራሳቸው በዶክተርነትና በፕሮፌሰርነት መሾማቸው መጋለጡ ይታወሳል። በኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ህግ የሃሰት ዲግሪና ሰርተፍኬት ተጠቅሞ ለራስም ሆነ ለሌሎች ጥቅም ማግኘትና ማስገኘት በማጭበርበር ወንጀል የሚያስከስ ስና እስከ አንድ አመት እስር የሚያሰቀጣ ድርጊት ነው።
የሴንቸሪ ዩኒቨርሲቲ ባለቤት ከዚህ በፊት የማጭበርበር ወንጀል ሲፈጽም ተደርሶበት በባለቤትነት ሲመራው የነበረው የሃዋይ ቢዝነስ ኮሌጅን እኤአ 2007 እንዲዘጋ ተደርጓል።
በኢፌዲሪ ህገ መንግስት መሰረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፍተኛው የስልጣን አካል ሲሆን አፈጉባኤው ዋነኛው ህግ አውጭ ተደርጎ ይቆጠራል። የዛሬ አራት አመት አፈጉባኤ ሆነው የተሾሙት አባዱላ ገመዳ ትምርታቸው ከ፰ኛ ክፍል አቋርጠው የደርግ ወታደር ሆነው የነበር ሲሆን በኤርትራ በሻቢያ ተማርከው የነበረ ሲሆን በህወሃትና በሻቢያ መካከል በተደረገ ስምምነት መሰረት ከ እነ አቶ ኩማ ደመቅሳ ጋር ለህወሃቶች ተላልፈው ከተሰጡ በሁዋላ የ ኦህዴድ መሪና መስራች እንዲሆኑ ተደርጓል።
የእነ አባዱላን ዲርጊት አሳፋሪ ሲሉ የገለጹት እውቁ ጋናዊው ምሁር ፕሮፌሰር ጆርጅ አይቴ እንዲህ አይነት እርካሽ የማጭበርበርና የማስመሰል ድርጊት የስር አቱን ንቅዘት ፍንትው አድርጎ አንደሚያሳይ ገልጸዋል። ፕሮፈሰሩ ተጠያቂነት የሌለው ህገውጥነት የ አንባገነኖች ባህሪ መሆኑን አስገንዝበው እንዲ አይነትኞቹ አጭበርባሪ የስልጣን ጥመኞች ለውጥ ፈላጊ በሆነው አዲስ ትውልድ መተካት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
አይቴ አገር ለመምራት የምያስፈልገው እውቀት እንጂ ዲግሪ አይደለም ብለዋል። “ዲግሪ መግዛት ይቻላል፣ እውቀት ግን ፈጽሞ አይገዛም” በማለት የእነ አባዱላን ድካም ከንቱነት ጠቁመዋል።
የቀድሞው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስቴር ዴታ የነበረው ኤርምያስ ለገሰ በበኩሉ አባዱላ በራስ መተማመን የሌለው የሃሰት ስብእና በህወሃቾች የተፈጠረለት ግለሰብ በመሆኑ ያንን በዲግሪ ጋጋታ ለመሸፈን የሚያደርገው ጥረት አካል ሊሆን እንደሚችል ግምቱን ሰንዝሯል።
በርካታ ዜጎች ያለምንም ወንጀልና ጥፋት ለበርካታ አመታት ያለፍርድ በእስር በሚሰቃዩባት ኢትዮጵያ እነ አባዱላ በሃሰት ዲግሪ
አገር ሲመሩ ማየት ህዝቡን የበለጠ ለለውጥ ሊያነሳስው ይገባል ሲል አስተያተቱ ሰጥቷል።
source.- http://www.zehabesha.com/amharic/archives/38893
Monday, 9 February 2015
የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥሰት ዙሪያ መከረ
ኢሳት ዜና
ህብረቱ ጥር 27፣2007 ዓም በብራሰልስ ቤልጂየም የአውሮፓ ህብረት ጽ/ቤት ውስጥ ለ3 ሰአታት ባደረገው የኢትዮጵያ የሰአብአዊ መብት ግምገማ በኦጋዴን ክልል እና በተቀሩት የኢትዮጵያ ግዛቶች በዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ሰቆቃ የአውሮፓ ህብረትና አባል መንግስታት በዝምታ መመልከታቸውን ማብቃት አለበት የሚል ውሳኔ አስተላልፈዋል።
ስብሰባውን ያዘጋጁት የህብረቱ የሶሻሊስትና የዲሞክራቲክ ፓርቲዎች ጥምር ህብረት ፣ ውክልና አልባ ህዝቦች ተቆርቋሪ ድርጅት ጋር በመተባበር ነው። በስብሰባው ላይ የኦጋዴን ክልል ፕሬዚዳንት አማካሪ የነበረና በክልሉ የሚፈጸመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት በመረጃ በማጋለጥ ላይ የሚገኘው ወጣት አብዱላሂ ሃሰን፣ ተቀማጭነቱ በጄኔቫ የሆነ የአፍሪካ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ባልደረባ፣ አቶ አብዱላሂ ሙሃመድ፣ የኦጋዴን ሴቶች ተወካይ ፣ ጋዜጠኛና የክሬት ትረስ ዳይሬክተር ግርሃም ፌብልስ፣ እንዲሁም በኦሮሞ ሴቶች ላይ የሚደረሰውን ሰቆቃ በማስመልከት ጥናት ያካሄዱት፣ ዶ/ር ባሮ ቀኖ በቪዲዮ የተደገፈ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል።
እንግሊዛዊው ግራሃም ፌብልስ በኢትዮጵያ 2 አመታት ቆይታቸው የታዘቡትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በተለይም በኦጋዴን ክልል በሴቶች ላይ ተፈጽሟል ያሉትን አስገድዶ መድፈር ወንጀል የታዳሚውን ስሜት በነካ መልኩ አቅርበዋል። በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በዜጎች ላይ ሽብርን እያካሄደ ነው ያሉት ሚ/ር ፌብልስ የዚህ ሰቆቃ ፈጻሚዎች፣ ከአውሮፓ ህበረትና መንግስታት በያመቱ ከፍተኛ የገንዘብ እርዳታ የሚያገኙ መሆናቸው እጅግ የሚያሳዝነው ነው ብለዋል።
በጉባኤው ላይ የኦጋዴን ነጻነት ግንባር ተወካይ ዶ/ር ባዳል አህመድ እና አርበኞች ግንቦት7 ተወካይ አቶ አበበ ቦጋለ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸመ ነው የሚሉትን የሰብአዊና የፖለቲካ መብቶች እረገጣና አስከፊ ሰቆቃ በእየተራ አቅርበዋል።
የአውሮፓ ህብረትን ወክለው በስብሰባው ላይ የተገኙት ወ/ሮ አና ጎሜዝና የእንግሊዝ የፓርላማ ተወካይ ወ/ሮ ጁሊ ዋርድ በየተራ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ መንግስት ከ60 በመቶ በላይ በጀቱን ከአውሮፓ ህበረት እየተቀበለ ዜጎች ላይ እየፈጸማቸው ያለው አስከፊ ሰቆቃዎችን አውሮፓ ካሁን በሁዋላ በዝምታ ማየት የለባትም ካሉ በሁዋላ፣ ኢትዮጵያኖች በአገራቸው እየተፈጸመ ያለውን አፈናና ጭቆና የውጭ ማህበረሰብ ያስቆምልናል ብለው ከመጠባበቅ ለራሳቸው ነጻነት ልዩነቶቻቸውን በማቻቻልና መለስተኛ ፕሮግራም በማዘጋጀት ህብረት ፈጥረው በአንድነት መታገልና ለለውጥ መነሳት አለባቸው ብለዋል።
የአውሮፓ ህብረት በዘንድሮው ምርጫ ላይ ታዛቢዎችን እንዳይልክ የወሰነው የኢህአዴግ መንግስት በየ 5 አመቱ የሚያደርገውን የተሳሳተ ምርጫ በማጀብ ህጋዊነት ለማሰጠት እንደከዚህ በፊቱ ለመተባበር ፈቃደኛ አለመሆኑን ለመግለጽ ሆኖ ሳለ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ግን ህበረቱ በገጠመው የበጀት ችግር ምክንያት ታዛቢ አልክም ብሎአል ብሎ የጀመረው ቅስቀሳ መሰረተ ቢስና የተለመደ ህዝብን የማዘናጊያ ወሬ እንደሆነ ገልጸዋል። የአመቱን 60 በመቶ የሚሸፍን በጀት የሚሰጠው ህብረቱ፣ ኢትዮጵያን የመሰለ ስትራቴጂክ አገር፣ ህብረቱ የገንዘብ እጥረት ገጥሞታል ብሎ ማሰብ ራስን እንደማታለል ይቆጠራል ብለዋል።
ህብረቱ ምርጫው ከመደረጉ ከሚቀጥለው ወር በፊት የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችንና ሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን በስፋት የሚያሳትፍ ትልቅ ጉባኤ በሚያዚያ ወር ላይ ለመጥራት በዝግጅት ላይ እንዳለ በዚህ ስብሰባ ላይ ተገልጿል።
አንዳንድ የፓርላማ አባላት በዚህ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ግብጽ ህዝብ ሆ ብሎ በመነሳት ከመጪው ግንቦት ምርጫ በፊት አምባገነንነትን ከራሱ ትከሻ ላይ ለማውረድ መነሳት አለበት ሲሉ ተናግረዋል ። የኢትዮጵያ መንግስት በሚቀርብበት የሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ አቋሙን እንዲገልጽ ቢጋበዝም ፣ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ የሆነ ቤልጂየማዊ ዜጋ የሆነ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ሰራተኛ የተገኘ ሲሆን ስራውም መረጃ መሰብሰብ እንጅ አስተያየት መስጠት አለመሆኑን ገልጾ፣ ምንም ንግግር ሳያደርግ ወጥቷል።
Sunday, 8 February 2015
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕድገት አለ ይላሉ፤ ተቃዋሚው እንደራሴ አይስማሙም
ዋሺንግተን ዲሲ - አዲስ አበባ—
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ፤ እንደራሴ ግርማ ሠይፉ፤ የኤርትራ ካርታ
የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት በ2006 ዓ.ም በ10.3 ከመቶ እያደገ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ለፓርላማው ባቀረቡት ሪፖርት አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት ሪፖርት በአጅጉ ያሣዘናቸው መሆኑን የገለፁት የተቃዋሚ ፓርቲው እንደራሴ ግርማ ሠይፉ ሪፖርቱ የሃገሪቱን እውነታ አያሣይም ብለዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት ላይ የተጠናቀረውን አጭር ዘገባና የእንደራሴ ግርማ ሠይፉን አስተያየት የያዘውን ፋይል ያዳምጡ
http://amharic.voanews.com/audio/2632451.html
Saturday, 7 February 2015
ኢትዮጵያዊያን ዋሺንግተን ላይ በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ደጅ ወጡ
ሕጋዊና ሕዝባዊ ድጋፍ ያላቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ማፍረስ ሰላማዊ ትግሉን አደጋ ላይ ይጥላል ያሉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያ ሠልፈኞች ዛሬ ዋሺንግተን ውስጥ በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደጅ ላይ ተሰልፈው ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሂደት ሀገርን የማይጠቅሙ አፈናዎች ቢበራከቱም ሰላማዊ ትግላችን ይቀጥላል ብለዋል ሠልፈኞቹ።
በዩናይትድ ስቴይትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ፊት ለፊት እጅግ የቀዘቀዘው የዋሽንግተን ዲሲ አየር ሳይበግራቸው የቆሙት ኢትዮጵያዊያን በዚህ የምርጫ ዓመት የኢትዮጵያ መንግሥት የዴሞክራሲ አፈናውን አጠናክሯል ሲሉ የተቃውሞ ድምፅ አሰምተዋል።
................ለዝርዝሩ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ,-http://amharic.voanews.com/
Friday, 6 February 2015
5 የአየር ሃይል የጥበቃ አባላትና 2 ፓይለቶች ጠፉ
ኢሳት ዜና :-የኢሳት የአየር ሃይል ምንጮች እንደገለጹት ከሁለት ሳምንት በፊት 5 የአየር ሃይል የጥበቃ አባላት እስከነ ሙሉ ትጥቃቸው እንዲሁም 2 ፓይለቶች ከድሬዳዋ አየር ሃይል ጠፍተዋል። የጥበቃ አባላቱም ሆነ ፓይለቶቹ ያሉበትን ለማወቅ የተደረገው ጥረት እስካሁን አልተሳካም። ይህንን ተከትሎ ጄ/ል ሳሞራ የኑስ ከመቶ አለቃ ማእረግ በላይ ያላቸውን አየር ሃይል አባላት ሰብስበው ግምገማ አካሂደው ነበር።
ጄ/ል ሳሞራ “የአየር ሃይል አባላት ለምን ይከዳሉ? አሁን ያላችሁትስ ምን ታስባላችሁ?” የሚል ጥያቄ ለተሰብሳቢው ያቀረቡ ሲሆን፣ የአየር ሃይል አባላቱም ከፍተኛ የሆነ የአስተዳደር በደል እንደሚደርስባቸው፣ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ክፍያ እንደሚከፈላቸው፣ በመኖሪያ ቤት እጦት እንደሚሰቃዩ ገልጸዋል። መኮንኖቹ በርካታ ችግሮችን ዘርዝረው ያቀረቡ ቢሆንም፣ ጄ/ል ሳሞራ ችግሮችን ከመስማት ውጭ ምንም አይነት ምላሽ ሳይሰጡ ሄደዋል።
የአየር ሃይል አባላት ሞራል ( ስሜት) መዳከም ገዢው ፓርቲ በሩሲያ ቅጥር አብራሪዎች ላይ እምነቱን እንዲጥል አድርጎታል። የትግራይ ተወላጅ የሆኑት ሻምበል ሳሙኤል ግደይ እና ቴክኒሻን ብርሃን ግደይ ከመቶ አለቃ ቢልልኝ ደሳለኝ ጋር በመሆን ስርአቱን አናገለግልም ብለው ሄሊኮፕተር ይዘው መጥፋታቸው፣ የህወሃትን የዘር ፖለቲካ መሰረት እንዳናጋው ምንጮች ይገልጻሉ። ለወትሮው ይታመኑ የነበሩ የትግራይ ተወላጅ የአየር ሃይል አባላት ሳይቀሩ የሚታመኑ ሆነው ባለመገኘታቸው ፣ ባለስልጣናቱ አይናቸውን የውጭ ቅጥረኞች ላይ እያዞሩ ነው።
ስርዓቱን አናገለግልም ብለው የጠፉት የአየር ሃይል አባላት የተቃዋሚ ድርጅቶችን ተቀላቅለው እየታገሉ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የአፍሪካ መሪዎችም ሆነ የሌሎች አገራት መንግስታት ለስብሰባ ወደ አዲስ አበባ በሚመጡበት ጊዜ ለደህንነት ስራም ሆነ ለልዩ ጥበቃ የሚመደቡት የአንድ ብሄር ተወላጆች ናቸው በማለት የሌሎች ክልሎች የደህንነት አባላት ቅሬታ ማሰማታቸው ታውቋል። የ24ኛው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ከተካሄደ በሁዋላ ለግምገማ ከተጠሩት ምድብተኛ የደህንነት ሰራተኞችና የጸጥታ አካላት መካከል አንዳንዶች፣ ” ለመሪዎችና ለእንግዶች ደህንነት የሚመደቡት ጠባቂዎች የአንድ አካባቢ ተወላጆች ብቻ መሆናቸው፣ “ስርአቱ የእናንተ አይደለም፣ አናምናችሁም” የሚል መልክት አለው በማለት በድፍረት ለገምጋሚዎች ተናግረዋል።
“በብሄራችን ምክንያት ተበድለናል” ያሉት የደህንነት ሰራተኞችና ጠባቂዎች፣ ደረሱብን ያሉዋቸውን በርካታ ችግሮች ዘርዝረው አቅረበዋል። ” በኢትዮጵያ ውስጥ አሸባሪዎች ራሳቸውን እያደራጁና መረባቸውን እየዘረጉ በመጡበት ሁኔታ የምናምነውን ሰው እንመድባለን” የሚል መልስ ግምገማውን ከሚመሩ መሪዎች የተሰጠ ሲሆን፣ ተሳታፊዎች በተሰጠው መልስ ማዘናቸውን በግምገማው የተሳተፉ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
- source.- satenaw.com
አሜሪካ ፡ - "ኢትዮጵያ በስርዓቷ የወደቀች አገር ናት" ዶክመንተሪ ቪዲዮውን ይመልከቱ የአሜሪካ ፖሊሲ እና የኢትዮጵያ መንግስት ክሽፈት
ኢትዮጵያ መስቀለኛ መንገድ ላይ ናት::ውስጣዊ የፖለቲካ የማህበራዊ ኢኮኖሚ እና የሃይማኖት ችግሮኝ አጣብቂኝ ውስጥ ናቸው::በአሁን ወቅት ስልጣን ላይ የመጣውን መንስት ተከትሎ ጎሳን ያማከሉ ግጭቶች ተስፋፍተዋል::ይህ መንግስት በስልጣን ላይ ለ24 አመታት ቆይቷል::መሰረቱም በጎሰኝነት ላይ ሲሆን አስተዳደሩንም የያዙት አነስተኛ የሆኑ በጎሳቸው የተደረጁ የአንድ ብሄር ቡድን መሪዎች ናቸው::በሃገሪቱ የሚገኘውን እያንዳንዱን የመንግስት እና የግል ሴንተሮችን የተቆጣጠረው በራሱ ብሄር ተወላጆች እጅ ስር አድርጎ ነው:: ወታደሩ ደህንነቱ ሃይማኖቶች እና የኢኮኖሚ አውታሮች በትግራይ ብሄር ቡድን በሆነው በሕወሓት ቁጥጥር ስር ውለዋል:: የአሜሪካ መንግስት ያስጠናውን ጥናት ከፊል ሪፖርት ዝርዝር ከዚህ በሚከተለው ቭድዮ ይመልከቲት::
የዞን ዘጠኞችን ጉዳይ የሚያዩት መሃል ዳኛ በራሳቸው ፍቃድ ችሎቱን ለቀቁ
(ኢ.ኤም.ኤፍ) የዞን ዘጠኝ ጦማርያንና ጋዜጠኞችን ጉዳይ የሚመለከተው የልደታው ችሎት ለተከታታይ ሁለት ቀናት የሚሰጠው ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል በጉጉት ሲጠበቅ ነበር። በተለይም ጦማርያኑ እና ጋዜጠኞቹ የመሃል ዳኛው ስራቸውን በሚገባ እያከናወኑ ስላልሆነ፤ እንዲነሱላቸው ነበር በደብዳቤ የጠየቁት። ይህ ጥያቄ ለፍርድ ቤቱ ሲቀርብ ዳኞቹ ያልጠበቁት ነገር በመሆኑ፤ በመገረም ነበር ደብዳቤውን ደጋግመው የተመለከቱት። በሁኔታው ላይ ከተነጋገሩ በኋላ፤ የመሃል ዳኛውን ውሳኔ ለማሳወቅ ለሚቀጥለው ቀን ጠዋት ቀጠሮ ሰጥተው ነበር ችሎቱ የተጠናቀቀው።
ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት አቤቱታ የመጀመሪያ ገጽ (ምንጭ፡ ዞን ዘጠኝ ድረገጽ)ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት አቤቱታ 2ኛ ገጽ (ምንጭ፡ ዞን ዘጠኝ ድረገጽ
በሚቀጥለው ቀን የሆነው ነገር ብዙዎችን ያስገረመ ነበር። የመሃል ዳኛው አቶ ሸለመ በቀለ ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል ማንም አላወቀም። በሚቀጥለው ቀን ሦስቱ ጋዜጠኞችና ስድስቱ ጦማሪያን በልደታ ፍርድ ቤት 19ኛ ምድብ ችሎት ቀረቡ። ዞን ዘጠኞች ከአንድ ቀን በፊት፤ ማለትም በ26/05/2007 ዓ.ም. “የመሀል ዳኛው አቶ ሸለመ በቀለ ይቀየሩልን” ሲሉ በፅሁፍ ያቀረቡት አቤቱታ፤ በግራ እና በቀኝ ዳኛው ውድቅ የተደረገ መሆኑ ተገለጸ። በዚህም መሰረት “የመሃል ዳኛው ይነሱልን” ጥያቄ በድምጽ ብልጫ መውደቁ ታወቀ። ሆኖም የመሃል ዳኛው አቶ ሸለመ በቀለ በራሳቸው ፍቃድ ከመሃል ዳኝነት ያነሱ መሆናቸውን ገለጹ። “በራሴ ፈቃድ ከችሎቱ እራሴን አንስቻለሁ” ብለው በፍርድ ቤቱ ውስጥ ለተገኙት በሙሉ ነው ግልጽ ያደረጉት።
በፎቶው ላይ እንደሚታየው የመሃል ዳኛው የሉም። ጉዳዩን የተመለከቱት የግራ እና ቀኝ ዳኞች ናቸው። ተከሳሾች ቆመው ጉዳያቸውን ለፍርድ ቤት ሲያስረዱ ይታያል። ኤዶም ካሳዬ አግባብ ያልሆነው ኢፍትሃዊ ሂደት በመቃወም ጸጉሯን ተላጭታ ነበር የቀረበችው።
ይህም ሆኖ ጥያቄውን ያቀረቡት ጋዜጠኞች እያንዳንዳቸው 500 ብር ሊቀጡ እንደሚገባ ከተነገራቸው በኋላ፤ ለአሁኑ ግን በይቅርታ መታለፋቸውን ነው ፍርድ ቤቱ የገለጸው። ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ከተከሳሾቹ መካከል አቤል ዋበላ እንደትላንት ከፍርድ ቤቱ ወደ ቅሊንጦ ማረሚያ ቤት ሲወሰድ፤ ፖሊሶቹ እረስተው በእጁ ካቴና ሳያስገቡ ቀርተው ነበር። ያለካቴና ቅሊንጦ ከደረሰ በኋላ ግን የደረሰበትን ስቃይ ሲያስረዳ በፍርድ ቤቱ ውስጥ የተገኙት በሙሉ አዝነው ነበር። “ቅሊንጦ ስንደርስ እጄ ላይ ካቴና ስላልነበረ፤ የማረሚያ ቤቱ ሰራተኞች እየሰደቡ እና እያንገላቱ እጄን በውሻ ሰንሰለት አስረው ነው ያሳደሩኝ” በማለት እንባ እየተናነቀው ነበር የተናገረው። “ሌላው ቀርቶ ማዕከላዊ እያለሁ በደረሰብኝ ከፍተኛ ድብደባ ምክንያት አንድ ጆሮዬ በደንብ አይሰማም። በመሆኑም ለመስሚያ የሚያገለግለኝን የጆሮ ማዳመጫዬንም ወስደውብኛል” በማለት የደረሰበትን ግፍ እና በደል አስረድቷል።
ዳኛው… ለምን ይሄ እንደተደረገ የቅሊንጦ ማረሚያ ቤት ተወካይ ምላሽ እንዲሰጥ ብለው ሲጠይቁ፤ የቅሊንጦ አዛሪዎች ተወካይ አጥጋቢ መልስ መስጠት ሳይችል ቀርቷል። በመሆኑም በሚቀጥለው ቀጠሮ ማረሚያ ቤቱ ምላሹን በጽሁፍ እንዲያቀርብ አዘዋል።
zone9በመጨረሻም ሂደቱን በፎቶ ሊያነሳ የሞከረ አንድ ሰው በፖሊሶቹ ታስሮ ስልኩን ከወሰዱበት በኋላ፤ ወደ ቅሊንጦ እስር ቤት በሚሄደው የእስረኞች መኪና ውስጥ፤ በራሳቸው ስልጣን ለሰአታት ያህል ካሰሩት በኋላ ለቀውታል።
የዞን ዘጠኞች ቀጣይ ቀጠሮ ለየካቲት 11 ወይም ፌብሩዋሪ 18፣ 2015 ሲሆን፤ በሚቀጥለው ቀጠሮ ሲገኙ ለ21ኛ ግዜ ይሆናል ማለት ነው።
Thursday, 5 February 2015
መንግስት በፌስ ቡክና በሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች ያሰማራቸው ሰዎች የተፈለገውን ውጤት ማምጣት አልቻሉም ተባለ።
ማህበራዊ ድረገጾች ላይ የመንግስትን መልካም ገጽታ ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊደርጉ ይችላሉ በሚል ተከታታይ ስልጠና ተሰጥቷቸው የነበሩት የህዝብ ግንኑነት ባለሙያዎች (ኮምኒኬተሮች) እና የመንግስት ባለስልጣናት፤የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አልቻሉም መባላቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖ ጠቆሙ፡፡
ለመንግስት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችና ለካድሬዎች በአቶ ሬድዋን ሁሴን በሚመራው የመንግስት ኮምኒኬሽን ጽ/ቤት አማካይነት ከአራት ወር በፊት በማህበራዊ ድረገጾች አጠቃቀምና በመንግስት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ ተከታታይ ስልጠና መሰጠቱ ይታወቃል።
ሰልጣኞቹ ፌስቡክን ጨምሮ በተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾች ላይ የመንግስትን አዎንታዊ ሚና አጉልተው በመጫወት የገጽታ ግንባታ ሥራ እንዲያከናውኑ የተሰማሩ ቢሆንም፤ እንደታሰበው ውጤት ሊያስገኙ አለመቻላቸው ተመልክቷል።
ጉዳዩን በቅርበት የኒያውቁ አካላት እንደሚሉት፦ውጤት ላለመገኘቱ ዋነኛው ምክንያት ብዙዎቹ “ኮምኒኬተሮች” በአቶ በረከት ስምኦን የሚኒስትርነት ዘመን ከየክልሉ በፖለቲካ ብቃት ብቻ ተመልምለው፣ በለብለብ ሥልጠና ወደሕዝብ ግንኙነት ሙያ የገቡከ መሆናቸው አኳያ ከፍተኛ የአቅም ችግር ስላለባቸው ነው።
ቀሪዎቹም በቤት አሰጣጥ፣ በደመወዝ ጭማሪና እና በመሳሰሉት ጉዳዮች በሚስተዋሉ አድሎአዊ የጥቅማጥቅም አሰጣጥ ያኮረፉ መሆናቸው ተገልጿል።
<<ኮምኒኬተሮቹ>> ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት በየመስሪያ ቤቱ ሲመደቡ ፤ ቀደም ሲል በየመስሪያ ቤቶቹ ከነበሩ ብቃት ካላቸው የኮምኒኬሽን ባለሙያዎች አንዳንዶቹ ከቦታቸው እንዲነሱ ሲደረግ ፤የተቀሩት በገዛ ፈቃዳቸው ሥራቸውን ለመልቀቅ ተገደዋል፡፡
አብዛኛዎቹ<<ኮምኒኬተሮች>> ከተሰጣቸው ሥልጠና በሁዋላ እንደፌስቡክ ባሉ ማህበራዊ ድረገጾች ላይ የራሳቸውን ወይንም የድርጅታቸውን አካውንት ለመክፈት ሙከራ ከማድረግ በዘለለ ምንም ማከናወን ሳይችሉ መቅረታቸው፤ የአቶ ሬድዋንን ቢሮ ማበሳጨቱ ተጠቁሟል፡፡
በተለይ በፌስቡክ የሚሳተፈውን ዲያስፖራ እና የተቃውሞ ሃይሉን በአንድ ላይ በመጨፍለቅ «አክራሪ ሃይሎች» በሚል የፈረጀው ኢህአዴግ ፤ይህን ሃይል ቢቻል ጸጥ ለማሰኘት ካሰማራቸው ስልጣኞች ባሻገር ከ25 በላይ የሚሆኑ ሚኒስትሮች ሳ ማህበራዊ ድረገጾችንእንዲጠቀሙ ሲወተውት ቆይቷል።
ይሁንና እስካሁን በግልጽ የራሳቸው አካውንት ያላቸው ባለስልጣናት በጣት የሚቆጠሩ ከመሆናቸው አኳያ ለኢህአዴግ እንቅፋት የሆነውን ሃይል የሚገዳደሩ አለመሆናቸው ቢሮውንና ኢህአዴግን እንዳሳሰበው ከኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡
source,-ethsat.com
አቶ ሲሳይ ዘርፉ የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላለፈበት
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
ህዳር 27 እና 28/2007 ዓ.ም በ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ተዘጋጅቶ ለነበረው የአዳር ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ የቅስቀሳ በራሪ ወረቅት ሲበትን ለእስር የተዳረገው የሰማያዊ ፓርቲ አባል አቶ ሲሳይ ዘርፉ ዛሬ ጥር 28/2007 ዓ.ም የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላፈበት፡፡
ታህሳስ 14/2007 ዓ.ም በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መናገሻ ምድብ 2ኛ ወንጀል ችሎት ቆርቦ የነበረው አቶ ሲሳይ ዘርፉ ‹‹…‹ነጻነት ለፍትሓዊ ምርጫ› ለመላው ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊ ሁሉ….ተብሎ የተጻፈበት በራሪ ወረቀቶች ለህብረተሰቡ ሲያከፋፍል እጅ ከፈንጅ በመያዙ በፈጸመው የሐሰት ወሬን በማውራት ህዝቡን ማነሳሳት ወንጀል…›› በሚል በፌደራል አቃቤ ህግ ለቀረበበት ክስ ያቀረበው የክስ መቃወሚያ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ መደረጉ ይታወሳል፡፡
ከዚህም ባሻገር አቶ ሲሳይ ዘርፉ ጥር 7/2007 ዓ.ም የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበርና ም/ሊቀመንበር የሆኑትን ኢ/ር ይልቃል ጌትነትና አቶ ስለሺ ፈይሳ እንዲሁም የኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ህብረት (ኦህዴህ) ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለን በመከላከያ ምስክርነት አቅርቦ የነበር ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ‹‹ምስክሮቹ ከወንጀል ድርጊቱ ጋር ቀጥተኛ የሆነ ምስክርነት ሳይሆን የራሳቸውን የፖለቲካ አመለካከት ሚዛናዊነት በጎደለው መልኩ ነው ያቀረቡት፡፡›› በሚል ምስክሮቹ የሰጡትን የምስክርነት ቃል ውድቅ አድርጓል፡፡
አቃቤ ህግም በተሰጠው የጥፋት ውሳኔ ላይ ‹‹ተከሰሽ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ 82(ሀ) 1/ መሰረት ማቅለያው ታይቶለት ከዚህ ቀደም የወንጀል ድርጊት ያልፈጸመ ስለሆነ የምንጠይቀው የቅጣት ማክበጃ የለንም፡፡ ሆኖም ግን በሰራው የወንጀል ድርጊት የመጨረሻው ጣሪያ ውሳኔ እንዲሰጥልን እንጠይቃለን፡፡›› ብሏል፡፡ ፍርድ ቤቱ ለካቲት 3/2007 ዓ.ም የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት በመናገሻ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል፡፡
አቶ ሲሳይ ዘርፉ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለበት ዕለት ጀምሮ ዋስትናው ተነፍጎ ቀደም ብሎ በፖሊስ ጣቢያና አሁን ደግሞ ቂሊንጦ እስር ቤት በእስር ላይ ይገኛል፡፡
Wednesday, 4 February 2015
ጸጉሯን ተላጭታ ፍርድ ቤት ቀረበች የዞን ዘጠኟ ጋዜጠኛ ኤዶም
የዞን ዘጠኟ ጋዜጠኛ ኤዶም ጸጉሯን ተላጭታ ፍርድ ቤት ቀረበች – “የእምነት ክህደት ቃላችንን ከመስጠታችን በፊት ዳኛው ይነሱልን” – ዞን ዘጠኞች
>በእነ ሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው የዞን ዘጠኝ ጦማርያንና ጋዜጠኞች ሰብሳቢ ዳኛው ከችሎት እንዲነሱ ጠየቁ፡፡
ጥር 26/2007 ዓ.ም ለ17ኛ ጊዜ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ልደታ ምድብ የቀረቡት ጦማርያኑና ጋዜጠኞቹ የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ የሆኑት አቶ ሸለመ በቀለ ‹‹የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብታችንን አላስከበሩልንም›› በሚል ከችሎት እንዲነሱ በጽሑፍ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የተሰየመው ተሻሽሎ ቀርቧል በተባለው የአቃቤ ህግ ክስ ላይ የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመስማት እንደነበር ዳኞቹ ቢናገሩም፣ ተከሳሾች አቤቱታ እንዳላቸው በመግለጽ የእምነት ክህደት ቃል ለመስጠት ዝግጁዎች አለመሆናቸውን ለችሎቱ ማስረዳት ችለዋል፡፡
ተከሳሾች ‹‹እኛ በሰብሳቢ ዳኛው ላይ አቤቱታ አለን፤ ፍርድ ቤቱ የራሱን ውሳኔ እንኳ አላከበረም፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን የእምነት ክህደት ቃላችንን ለመስጠት ዝግጁዎች አይደለንም›› በሚል ፍርድ ቤቱ አቤቱታቸውን እንዲቀበል ጠይቀዋል፡፡
ዳኛ ሸለመ በቀለ ‹‹ፍርድ ቤቱ ቃሉን አላከበረም›› በሚለው ጉዳይ ላይ መልስ ሲሰጡ ‹‹የእኛን ውሳኔ የማትቀበሉ ከሆነ ጉዳዩን በይግባኝ እንዲታይ ማድረግ ይቻላል›› ብለዋል፡፡
‹‹ላለፉት ስድስት ወራት በነበረው የክርክሩ ሂደት የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ አቶ ሸለመ በቀለ ሂደቱን በአግባቡ በመምራት የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብታችንን አላስጠበቁልንም፡፡ በተለያየ ጊዜም ሐሳባችን ለመግለጽ ስንሞክር ክልከላ አድርገውብናል፡፡ አሁን ደግሞ ችሎቱ ራሱ የሰጠውን ትዕዛዝ ራሱ ሽሮ ፈጽሞ ልንረዳው በማንችለውና የመከላከል መብታችንን በሚያጣብብ የክስ ሁኔታ ክርክሩን እንድንቀጥል ሲበየንብን የችሎቱ ሰብሳቢ ወሳኝ ሚና ነበራቸው›› ሲሉ ተከሳሾች በሰብሳቢ ዳኛው ላይ ቅሬታቸውን በአቤቱታቸው ገልጸዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ አቶ ሸለመ በቀለ ከችሎት እንዲነሱ የሚጠይቀውን አቤቱታ አይቶ ነገ ብይን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
............SOURCE,- http://www.zehabesha.com/
መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ እስር ቤት ውስጥ በደረሰባቸው ችግር ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ እኚህ ነበሩ
የህዳር 27/28 የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የጠራው የአዳር ሰልፍ ወቅት ተይዘው በደረሰባቸው ከፍተኛ ድብደባ እና ለሶስት ቀን የስኳር በሽታ መድሃኒት እንዳይገባላቸው በመከልከላቸው ለህመም የተዳረጉት የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) ምክትል ፀኃፊ መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ ከእስር ከተፈቱበት ጊዜ ጀምሮ ለሁለት ወር ሆስፒታል ከቆዩ በኋላ በዛሬው ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ በአዳሩ ሰላማዊ ሰልፍ ወቅት ተይዘው ከፍተኛ ድብደባ የደረሰባቸው ሲሆን ለአምስት ቀናት ቀዝቃዛና ጨለማ ቤት ውስጥ ታስረው ቆይተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከታሰሩበት ጊዜ ጀምሮ ይዘውት የነበረውን የስኳር በሽታ መድሃኒታቸውን በመቀማታቸው፣ እንዳይገባላቸው በመከልከላቸውና በወቅቱም ህክምናም ባለማግኘታቸው ለከፍተኛ ህመም በመዳረጋቸው ለሁለት ወር ያህል ዘውዲቱ ሆስፒታል ቆይተዋል፡፡
መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ እስር ቤት እያሉ በደረሰባቸው ችግር ምክንያት ዘውዲቱ ሆስፒታል ከገቡበት ታህሳስ 4/2007 ዓ.ም ጀምሮ ከፍተኛ ህመም እየተሰቃዩ እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የመቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ የቀብር ስነስርዓት ዛሬ ጥር 27/2007 ዓ.ም በቦሌ ሚካኤል እንደሚፈጸም ለማወቅ ተችሏል፡፡
source,-http://ethioforum.org/amharic/
Tuesday, 3 February 2015
35 ሰዎች ቀይ ባህር ውስጥ ጠፉ * የ9 ኢትዮጵያውያንን ሰውነት አግኝተዋል
35 ሰዎች ቀይ ባህር ውስጥ ጠፉ * የየመን ነብስ አድን ሰራተኞች የ9 ኢትዮጵያውያንን ሰውነት አግኝተዋል
ዘ-ሐበሻ) ዜግነታቸው ከኢትዮጵያ ሶማሊያና አካባቢው ሃገራት እንደሆነ የሚገመት 35 አፍሪካውያን ቀይ ባህር ውስጥ ይጓዙበት የነበረችው ትንሽዬ ጀልባ ሰጥማ የት እንደደረሱ ሊታወቅ አለመቻሉን የየመን ባለስልጣናት አስታወቁ::
በደቡባማው የየመን ክፍል ቲያዝ አቅራቢያ በሚገኘው የቀይባህር ውስጥ ሰጥመዋል ስለተባሉት አፍሪካውያን የየመኑ ባለስልጣን ጀነራል ሰኢድ ስባሪ ሲናገሩ እነዚህ ሰደተኞች በባህር ላይ ይጓዙ የነበረው 49 ሆነው ሲሆን በነበረው መጥፎ አየር የተነሳ ሊሰጥሙ ችለዋል:: እንደ ጀነራሉ ገለጻ የየመን መንግስት የ13 ሰዎችን ሰውነት ያተረፈ ሲሆን 9ኙ የኢትዮጵያውያን እንዲሁም 5ቱ የሶማሊያውያን ነው ተብሏል::
እንዲህ ያለው አሰቃቂ አደጋ በየመን አካባቢ ሲደርስ በ6 ወር ጊዜያት ውስጥ ለ3ኛ ጊዜ ሲሆን ባለፈው ዲሴምበር 12 የየመን መንግስት የ24 ኢትዮጵያውያንን አስከሬን ከባህር እንዳወጣ; እንዲሁም በጁላይ 12 70 ኢትዮጵያውያን እንዲሁ በቀይ ባህር ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ዘ-ሐበሻ መዘገቧ አይዘነጋም::
እንደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት መግለጫ በዚሁ በቀይባህር በኩል ተሻገረው ወደ የመን ከሚሄዱ አፍሪክውያን መካከል በሺህዎች የሚቆጠሩት ሕይወታቸው በአንድ ዓመት ውስጥ ያልፋል::
- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/
ሰበር ዜና – የአንድነት አባላት በይፋ ሰማያዊ ፓርቲን ተቀላቀሉ
(ሰማያዊ ፓርቲ) ብሄራዊ ምርጫ ቦርድና ኢህአዴግ በወሰኑብን ፖለቲካዊ ውሳኔ ምክንያት አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን ተነጥቀናል ያሉ የአንድነት ፓርቲ አባላት› በይፋ ሰማያዊ ፓርቲን መቀላቀላቸውን አስታወቁ፡፡
በእነ በላይ ፍቃዱ አመራርነት አንድነት ፓርቲን በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ሲመሩ የነበሩ አመራሮች ዛሬ ጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ከቀድሞ ፓርቲያቸው አንድነት ጋር የፕሮግራምም ሆነ የስትራቴጂ ተመሳሳይነት ወዳለው ሰማያዊ ፓርቲ ተቀላቅለው ሰላማዊ ትግላቸውን ለመቀጠል መወሰናቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡
መግለጫውን የ‹ቀድሞው አንድነት ፓርቲ› አፈ ጉባዔ የነበሩት አቶ አበበ አካሉ፣ ምክትል አፈ ጉባዔው አቶ ፀጋዬ አላምረው፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ነገሰ ተፋረደኝ እንዲሁም የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊው አቶ ስንታየሁ ቸኮል ሌሎችን በመወከል ሰጥተዋል፡፡
‹‹የምናምነው በሰላማዊ ትግል ብቻ ነው፡፡ ይህን ሰላማዊ ትግል ለመምራት ደግሞ ሰማያዊ ፓርቲ ብቁ ነው ብለን በማመን ፓርቲውን ተቀላቅለናል›› ብለዋል በመግለጫው ላይ የተወከሉት አዲሶቹ የሰማያዊ አባላት፡፡
በዚህ መሰረትም በርከት ያሉ አመራሮችና አባላት በይፋ የሰማያዊ ፓርቲ የአባልነት ፎርም ሞልተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአንድነት አባላት ሰማያዊ ፓርቲን መቀላቀላቸውን አስመልክቶ መግለጫ ለመስጠት ወደ ሰማያዊ ቢሮ ባቀኑበት ወቅት ፖሊስ ሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ ድረስ በመግባት ‹‹በሰማያዊ ስም መግለጫ የሚሰጡ አካላት እንዳሉ ሰለሰማን ነው›› በሚል ለፓርቲው አመራሮች ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡
..........................
source,-http://ecadforum.com/
Monday, 2 February 2015
አባዱላ ገመዳ በሚኒሶታ ቅሌትን ተከናነቡ
አባዱላ ገመዳ በሚኒሶታ ቅሌትን ተከናነቡ (በሬስቶራንት ውስጥ የደረሰባቸውን የውርደት ቪድዮ ይዘናል)
aba dula
(ዘ-ሐበሻ) በምሽትና በድብቅ ሀሙስ ምሽት ሚኒሶታ የገቡት የሕወሓት ተላላኪው ባለስልጣን አባዱላ ገመዳ በሚኒሶታ ቅሌትን መከናነብ የጀመሩት ገና ከአውሮፕላን ከወረዱ ጀምሮ ነበር::
አባዱላ የሕወሓት ተላላኪ ሆነው የኢትዮጵያን እመራታለሁ እያሉ ከኤርፖርት የተቀበሏቸው ጥቂት ሶማሊያውያን የታክሲ ሾፌሮች ናቸው:: እነዚህ የሱማሊያ ታክሲ ሾፌሮች አባዱላን ከተቀበሉ በኋላ ብሎሚንገተን በተሰኘው የሚኒሶታ ከተማ ሂልተን ሆቴል ያሳረፏቸው ሲሆን እንደዚህ ቀደሙ የወያኔ ተላላኪዎች ሲመጡ ፖስተር ተለጥፎ ስብሰባ እንደሚጠራው ለአባዱላ የወያኔ ተላላኪዎች ያደረጉት ነገር የለም:: ይልቁንስ በቴክስት መልክት ብቻ በስልክ የወያኔ ኔትወርኮች ብቻ እንዲጠራሩ የተደረገና ሌላው ሕዝብ የአባዱላን ስብሰባ እንዳይሰማ ለማድረግ ጥረት ቢደረግም ይህ ቴክስት መልዕክት ለኢትዮጵያን ደረሰ::
ኢትዮጵያውያኑ ልክ እንደሕወሓት ተላላኪዎች ድምፃቸውን ሳያሰሙ በቴክስት መልዕክት የተጠራሩ ሲሆን ስብሰባው የሚደረግበት ሂልተን ሆቴል ተገኝተዋል:: አባዱላ ገመዳ ከአንዲት ሴት ጋር ሁለተኛ ፎቅ ላይ ቁጭ ብለው ወደታች በአንደኛው ፎቅ በኩል የሚገቡትን ሰው እየተመለከቱ; አጠገባቸው ያለችው የትግራይ ተወላጅ የሆነች ሴት የሰውን ማንነት የምትነግር ይመስል ለባለስልጣኑ ትጠቁማለች::
በዚህ መሃል የዘ-ሐበሻ አዘጋጆችም ሲገቡ ሴትየዋ ለአባዱላ በጥቆማ ስታሳይ የዘ-ሐበሻ አዘጋጆች ተመልክተዋል:: የዘ-ሐበሻ አዘጋጆች ወደ ስብሰባው ሊገቡ ሲሉ እንደተለመደው የተከለከሉ ሲሆን ስብሰባውን ያዘጋጀው አካል ከ30 በላይ የሚቆጠሩ ፖሊሶችን በመቅጠር ተቃዋሚ የሆኑ ሰዎች እንዳይገቡ ተከልክለዋል:: አንድ ፖሊስን በሚኒሶታ ለአንድ ዝግጅት በሰዓት መንግስት ከሚከፍለው በተጨማሪ ዝግጅት አዘጋጁ ከ$50 ዶላር ያላነሰ የሚከፍል ሲሆን የሕወሓት መንግስት ለነዚህ የአሜሪካ ፖሊሶች ለ6 ሰዓታት ለ እያንዳዳቸው $300 ዶላር በአጠቃላይም ለፖሊስ 9 ሺህ ዶላር አውጥቷል:: ይህም በኢትዮጵያ ብር ሲመነዝር 180 ሺህ ብር መሆኑ ነው:: ለአዳራሽ በትንሹ ከ2 ሺህ ዶላር በላይ, ለሶማሌ ታክሲ ሾፌሮች በሰዓት ከ60 ዶላር በላይ እንዲሁም ለአባዱላ እና ለተላላኪዎቻቸው የሆቴል አዳር ከ150 ዶላር በላይ የወጣበት ይኸው የሚኒሶታ ስብሰባ ካለስኬት የተጠናቀቀ ሲሆን በስበባው የተገኘው ሕዝብም ከ45 ሰው እንደማይበልጥ በውስጥ ጉዳዩን እንዲከታተሉ የላክናቸው ምንጮች አስታውቀዋል::
የሕወሃት መንግስት ተላላኪው አባዱላ ገመዳ በሚኒሶታ ስብሰባ እንዲያደርግ ግማሽ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ያጠፋ ሲሆን ያተረፈው ጥፋትን ብቻ ሳይሆን አባዱላ ገመዳ በሄዱበት ቦታ ሁሉ ስድበንም ጭምር ነው:: በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያን በሂልተን ሆቴልና በተለያዩ አባዱላ በሄዱባቸው የኢትዮጵያ ሬስቶራንቶች በመገኘት አባዱላን በሰብ አዊ መብት ረገጣ, በአፋኝነት, በአምባገነንነት, በሙስና እና በግድያ ወንጀሎች ሲናገሯቸውና በርሳቸው ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ሲያሰሙባቸው ውለዋል:: በአጠቃላይ የሕወሓት መንግስት የዲያስፖራ ሳምንት በኦሮሚያ አከብራለሁ ብሎ ስብሰባ የጠራበት የአባዱላ ስብሰባ ከትርፉ ኪሳራው አመዝኗል:: ኢትዮጵያውያኑም በሚኒሶታ በተቃውሞ ሲያሸብሩት ውለዋል::
አባዱላ ገመዳ ዛሬ በሚኒሶታ የደረሰባቸው ቅሌት ነገ በሲያትል እንደሚደገም ይጠበቃል:: በሲያትል ያሉ ኢትዮጵያውያን የአባዱላን የህወሃት ተልኮ ለማክሸፍ እየተጠባበቁ እንደሆነ የደረሰን መረጃ ያመለክታል:: አባዱላ በሬስቶራንት ውስጥ የደረሰባቸውን የተቃውሞ ውርደት ቭዲዮ ይመልከቱ::
- .....See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/38630#sthash.EKn2EcYu.xbNHJn76.dpuf
Subscribe to:
Posts (Atom)