Friday, 6 February 2015

የዞን ዘጠኞችን ጉዳይ የሚያዩት መሃል ዳኛ በራሳቸው ፍቃድ ችሎቱን ለቀቁ

(ኢ.ኤም.ኤፍ) የዞን ዘጠኝ ጦማርያንና ጋዜጠኞችን ጉዳይ የሚመለከተው የልደታው ችሎት ለተከታታይ ሁለት ቀናት የሚሰጠው ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል በጉጉት ሲጠበቅ ነበር። በተለይም ጦማርያኑ እና ጋዜጠኞቹ የመሃል ዳኛው ስራቸውን በሚገባ እያከናወኑ ስላልሆነ፤ እንዲነሱላቸው ነበር በደብዳቤ የጠየቁት። ይህ ጥያቄ ለፍርድ ቤቱ ሲቀርብ ዳኞቹ ያልጠበቁት ነገር በመሆኑ፤ በመገረም ነበር ደብዳቤውን ደጋግመው የተመለከቱት። በሁኔታው ላይ ከተነጋገሩ በኋላ፤ የመሃል ዳኛውን ውሳኔ ለማሳወቅ ለሚቀጥለው ቀን ጠዋት ቀጠሮ ሰጥተው ነበር ችሎቱ የተጠናቀቀው። ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት አቤቱታ የመጀመሪያ ገጽ (ምንጭ፡ ዞን ዘጠኝ ድረገጽ)
ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት አቤቱታ 2ኛ ገጽ (ምንጭ፡ ዞን ዘጠኝ ድረገጽ በሚቀጥለው ቀን የሆነው ነገር ብዙዎችን ያስገረመ ነበር። የመሃል ዳኛው አቶ ሸለመ በቀለ ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል ማንም አላወቀም። በሚቀጥለው ቀን ሦስቱ ጋዜጠኞችና ስድስቱ ጦማሪያን በልደታ ፍርድ ቤት 19ኛ ምድብ ችሎት ቀረቡ። ዞን ዘጠኞች ከአንድ ቀን በፊት፤ ማለትም በ26/05/2007 ዓ.ም. “የመሀል ዳኛው አቶ ሸለመ በቀለ ይቀየሩልን” ሲሉ በፅሁፍ ያቀረቡት አቤቱታ፤ በግራ እና በቀኝ ዳኛው ውድቅ የተደረገ መሆኑ ተገለጸ። በዚህም መሰረት “የመሃል ዳኛው ይነሱልን” ጥያቄ በድምጽ ብልጫ መውደቁ ታወቀ። ሆኖም የመሃል ዳኛው አቶ ሸለመ በቀለ በራሳቸው ፍቃድ ከመሃል ዳኝነት ያነሱ መሆናቸውን ገለጹ። “በራሴ ፈቃድ ከችሎቱ እራሴን አንስቻለሁ” ብለው በፍርድ ቤቱ ውስጥ ለተገኙት በሙሉ ነው ግልጽ ያደረጉት።
በፎቶው ላይ እንደሚታየው የመሃል ዳኛው የሉም። ጉዳዩን የተመለከቱት የግራ እና ቀኝ ዳኞች ናቸው። ተከሳሾች ቆመው ጉዳያቸውን ለፍርድ ቤት ሲያስረዱ ይታያል። ኤዶም ካሳዬ አግባብ ያልሆነው ኢፍትሃዊ ሂደት በመቃወም ጸጉሯን ተላጭታ ነበር የቀረበችው። ይህም ሆኖ ጥያቄውን ያቀረቡት ጋዜጠኞች እያንዳንዳቸው 500 ብር ሊቀጡ እንደሚገባ ከተነገራቸው በኋላ፤ ለአሁኑ ግን በይቅርታ መታለፋቸውን ነው ፍርድ ቤቱ የገለጸው። ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ከተከሳሾቹ መካከል አቤል ዋበላ እንደትላንት ከፍርድ ቤቱ ወደ ቅሊንጦ ማረሚያ ቤት ሲወሰድ፤ ፖሊሶቹ እረስተው በእጁ ካቴና ሳያስገቡ ቀርተው ነበር። ያለካቴና ቅሊንጦ ከደረሰ በኋላ ግን የደረሰበትን ስቃይ ሲያስረዳ በፍርድ ቤቱ ውስጥ የተገኙት በሙሉ አዝነው ነበር። “ቅሊንጦ ስንደርስ እጄ ላይ ካቴና ስላልነበረ፤ የማረሚያ ቤቱ ሰራተኞች እየሰደቡ እና እያንገላቱ እጄን በውሻ ሰንሰለት አስረው ነው ያሳደሩኝ” በማለት እንባ እየተናነቀው ነበር የተናገረው። “ሌላው ቀርቶ ማዕከላዊ እያለሁ በደረሰብኝ ከፍተኛ ድብደባ ምክንያት አንድ ጆሮዬ በደንብ አይሰማም። በመሆኑም ለመስሚያ የሚያገለግለኝን የጆሮ ማዳመጫዬንም ወስደውብኛል” በማለት የደረሰበትን ግፍ እና በደል አስረድቷል። ዳኛው… ለምን ይሄ እንደተደረገ የቅሊንጦ ማረሚያ ቤት ተወካይ ምላሽ እንዲሰጥ ብለው ሲጠይቁ፤ የቅሊንጦ አዛሪዎች ተወካይ አጥጋቢ መልስ መስጠት ሳይችል ቀርቷል። በመሆኑም በሚቀጥለው ቀጠሮ ማረሚያ ቤቱ ምላሹን በጽሁፍ እንዲያቀርብ አዘዋል። zone9በመጨረሻም ሂደቱን በፎቶ ሊያነሳ የሞከረ አንድ ሰው በፖሊሶቹ ታስሮ ስልኩን ከወሰዱበት በኋላ፤ ወደ ቅሊንጦ እስር ቤት በሚሄደው የእስረኞች መኪና ውስጥ፤ በራሳቸው ስልጣን ለሰአታት ያህል ካሰሩት በኋላ ለቀውታል። የዞን ዘጠኞች ቀጣይ ቀጠሮ ለየካቲት 11 ወይም ፌብሩዋሪ 18፣ 2015 ሲሆን፤ በሚቀጥለው ቀጠሮ ሲገኙ ለ21ኛ ግዜ ይሆናል ማለት ነው።

No comments:

Post a Comment