.የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ፣ ግንቦት7 እና የአማራ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ ወደ ውህደት የሚያደርሳቸውን ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር፣ የግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ እንዲሁም የአማራ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ በጋራ ባወጡት መግለጫ ”ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ካሉበት አዘቅት በማውጣት ሕዝቡ የስልጣን ባለቤት የሚሆንበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የጋራ ትግልና መስዋዕትነት የግድ የሚለን ደረጃ ላይ ደርሰናል” ብለዋል። ድርጅቶቹ አያይዘውም ”አገራችንና ሕዝባችንን ከአዘቅት ለማውጣት በመጣመር ብቻ ሳይሆን በውህደት አንድ ሆነን አገራችንንና ሕዝባችንን አንድ በማድረጉ ረገድ አስፈላጊው መስዋዕትነት በመክፈል የትግል እድሜ እናሳጥር በሚል ለውህደት የሚያደርሰንን ውይይት ለመጀመር የሚያስችል ሂደቶችን አጠናቀን ወሳኝ ወደሆነው ሂደት ውስጥ መግባታችንን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና ወዳጆች ማብሰር እንፈልጋለን።” ብለዋል።

ከዚህ በሁዋላ በሚኖረው የሽግግር ሂደት ወቅትም በሁሉም የትግል ዘርፍ በጋራ መሥራት መጀመራቸውን ድርጀቶቹ ገልጸዋል። የውህደቱን ስምምነት የሶስቱ ድርጀቶች ተወካዮች፣ ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ መልካም ዜና መሆኑን ተናግረዋል። የውህደት ስምምነቱ የኢትዮጵያን ህዝብ የሚወክል ነው ያሉት የአርበኞች ግንባር የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አርበኛ መንግስቱ ወ/ስላሴ ”ትግላችን መስዋትነትን በሚጠይቅ ትግል ላይ የተመሰረተ መሆኑ ውህደቱን ኢትዮጵያዊ ያደርገዋል” ብለዋል። ሶስቱም ድርጅቶች የኢትዮጵያ ህዝብ ትግሉን እንዲደግፍ በተለይም የመከላከያ ሰራዊት አባላት አዲሱን ውህድ ሃይል ተቀላቅለው ለዲሞክራሲ፣ ለእኩልነትና ለነጻነት የሚደረገውን ትግል እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር በወያኔ ወታደሮች ላይ የተለያዩ ጥቃቶችን እየፈጸመ ይገኛል። ይህ የውህደት መስመር ስምምነትም ይህን የተጀመረውን መራራ ትግል ወደ አንድ በማምጣት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ስራ ለመስራት የሚያስችል ይሆናል።
source,-http://sebhatamare.wordpress.com
No comments:
Post a Comment